Categories
Uncategorized

መመዝገብ መመዝገብ መመዝገብ

ስም አልባ የክዊር ኢትዮጲያዊያንን ታሪክ ፣ ባህል ፣ ማንነት እና የቀን ከቀን ህይወትን የሚዳስስ ሀገር በቀል ማህበር ነው ። 

ክዊር ለሚለው ቃል ቀጥተኛ እና ገላጭ የሆነ የአማርኛ ትርጉም  በማጣችን እ. ኢ. አ. በ1993 የወንድ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች የተለያየ የመገናኛ ዘዴዎችን ለመፍጠር ብለው በመሰረቱት ያሆ ግሩፕ ( yahoo group ) ላይ በፈጠሩት የመገናኛ ገፅ ማንነታችንን ይገልጻል ብለው በማሰብ ዜጋ የሚለውን ቃል ተጠቅመዋል ። 

እኛም ወደፊት ማህበረሰባችንን አማክረን ሁላችንንም የሚያስማማ የአማርኛ ቃል እስከምናገኝ ድረስ ዜጋ የሚለውን ቃል ወርሰነዋል ። ይህን ርዕስ በቅርቡ የወጣው ነኝ ፖድካስት በደንብ ስለሚያብራራው መገኛውን እንደ መረጃ አያይዘነዋል ። 

ስም አልባን ለመመስረት ስንነሳ ሦስት መሰረታዊ ነጥቦችን ታሳቢ አድርገን ነው ፤ 

  • የመጀመሪያው ተደብቆ የቆየውን የዜጋውን የማህበረሰባችንን ታሪክ ፣ ማንነት እና ህልውና በግልፅ በማቅረብ እኛ ጋር ያለውን እውነታ ለሃገራችን ብሎም ለተቀረው የዓለም ክፍል ለማሳወቅ ነው ።  ይህም በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት በእውነተኛ እና ነባር በሆኑ ታሪካችን ለመተካት ነው ። 
  • ሁለተኛው ህልማችን ኢትዮጲያ ውስጥ ያሉ ዜጋ የሥነጥበብ ባለሙያዎችን ቦታ በመስጠት ያለንን የጥበብ ተሰጥኦ ያለምንም ገደብ ለማሳየት የታቀደ ነው ። 
  • ሦስተኛው አላማችን በሃገራችን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ያለውን ሚዛናዊ ያልሆነ ፣ አድሎአዊ እና እውነታን ያላማከለ የዘገባ ልምድን ለመቀየር የተነሳ ነው ። ስም አልባ ይህንን አሰራር ለመቀየር እኩል ፣ እውነተኛ ፣ ተኣማኒ እና የተጠና የመገናኛ ብዙኃንን በመፍጠር የተደራጀ ብሎም የነቃ የዜጋ ማህበረሰብ መፍጠርን እንደ ግብ አድርጎ ይዘወራል ። ይህንንም ለማሳካት የተለያዩ ዜጋ የፈጠራ ባለሙያዎችን እና የተለያየ የስነጥበብ እና ዕደጥበብ ስራዎቻቸውን በየጊዜው እንዲያቀርቡ የተለያዩ እድሎችን ያመቻቻል። 

እ. ኢ. አ. በ2022 የድህረ ገፃችንን እና የማህበራዊ ሚዲያዎቻችንን ይዘን  ታደሙልን ብለን ቀርበናል ። የመጀመሪያ እርምጃችንን ስንጀምር ታሪክን በአግባቡ መመዝገብ (DOCUMENTATION) የሚለውን ብሂል እንደ ዋነኛ መነሻ አድርገን ነው። 

ምንም እንኳን በሃገራችን የዜጋውን ማንነት እንደ ህገወጥ ብሎም በባህልም ሆነ ብዙ ቦታ በሚሰጣቸው እምነቶች እና የእምነት ተቋማት የተወገዘ ቢሆንም ታሪካችንን መመዝገብ ለወደፊት የህልውና ጥያቄ ዋነኛው ግብዓት  ነው ብለን እናምናለን ። ይህንንም ለማሳየት “ታሪካችንን መመዝገብ” የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ ታደሙልን ብለን በመጣንበት ወር የዜጋውን ህይወት ብሎም በአጠቃላይ የኢትዮጲያ የስነጥበብ መዝግቦ ማቆየት ልምዳችን ልናጋራችሁ ወደናል ። 

ድህረገፃቻን የተለያዩ የዜጋ ታሪኮችን እንደወረደ ከማቅረቡም በላይ ፤ በተለያዩ ባለሙያዎች የተጠኑ የጥናት እና ምርምር ጽሑፎችን ፣ ወጎችን ፣ መጣጥፎችን እና የስነ ጥበብ ትብብሮችን ፣ የፖሊሲ ማብራሪያዎች ብሎም በአለም ላይ ያለፉ የዜጋ የሰብአዊ መብት እንቅስቃሴዎችን ታሪክ እና ውጤታቸውን ያቀርባል ። ይዘክራል ። 

በዚህ የመጀመሪያ አምዳችን “በልግ” በሚል ርዕስ በ1958 ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ካሳተመው የቲያትር  ጫወታ ላይ መግቢያ ብሎ ያቀረባትን አጭር ፅሁፍ በአፄ ሃይለስላሴ ግዜ የነበረውን የመገናኛ ብዙሃን እና የስነጥበብ የመግለፅ መብት ውስንነትን ያሳያል ብለን በማሰብ ተጠቅመነዋል ። 

ምንም እንኳን ይህ ፅሁፍ ከተፃፈ ብዙ አስርት ዓመታት ቢያልፉትም ሀገራችን ይህንኑ ራስን የመግለፅ መብት መገደብ አሁንም በሰፊው ታስተናግዳለች ። በዚህም ምክንያት ይህ ፅሁፍ ልንፈጥረው እና ልናሳድገው ከምንፈልገው ጤናማ የመገናኛ ብዙሃን ግንባታ ጋር ስለሚገናኝ ለዚህ የመጀመሪያው አምዳችን ለግብዓትነት መርጠነዋል። 

ምንም እንኳን እንደ ባህል ሆኖብን እየተደማመጥን መስማማት ፣ መማማር እና አብሮ ማደግ እንዲሁም እራሳችንን በሌላው ጫማ አድርጎ ማየት ያልተለመደ ቢሆንም ፤ በራችን ለአዲስ ሃሳብ እና አብሮ ለመስራት ሁሌም ክፍት ነው ። አንብቡልን ፣ ታደሙልን ፣ እናም የሚያሳድግ እና ገንቢ አስተያየታችሁን ለግሱን ። ህልማችን የጠነከረ ፣ የነቃ እና የተደራጀ የዜጋ ማህበረሰብ ፈጥረን  ታሪካችን እንዲሁም ህልውናችንን ማወደስ እንደመሆኑ መጠን የማህበረሰባችንን የነቃ ተሳትፎ እጅጉን አድርገን እናበረታታለን። 

ወደፊት በጊዜ ሂደት ዳቦ ቆርሰን ስም አውጥተን እራሳችንን ለህዝባችን እስክናቀርብ ድረስ ስም አልባ ስማችን ከፍ ሲልም አለን የምንልበት መድረካችን ይሆናል።

“በ 1952 ዓ.ም. በየካቲት ወር “የሾህ አክሊልን” በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴያትር አቅርቤ እንዳበቃሁኝና ለጊዜው ስለምን እንደምጽፍ ጠንቅቄ ስላላወቅሁት ሃሳቤን በእግረ – ሕሊና ስመላለስበት ቆየሁ ፣ ከሐምሌ አጋማሽ እስከ ነሐሴ መነሻ ጅማ ከተማ በነበርኩበት የዕረፍት ጊዜዬ ውስጥ “በልግን” ጽፌ ጨርሼ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ ። 

በ 1953 ዓ.ም. ከሎንደን እንደመጣሁ ለመጀመሪያ ጊዜ “በልግን” በቀዳሚያው ኃይለ ሥላሴ ቴያትር አዳራሽ ለማቅረብ ሞከርኩ ፣ በአንዳንድ የአስተዳደር መሰናክል ምክንያት አልሆነልኝም ። ከብዙ ጥረት በኋላ መስከረም 19 ቀን 1954 ዓ.ም. ዓርብ ማታ ተከፈተ ። በማግስቱ መስከረም 20 ቀን ቅዳሜ ቀን እንዳይታይ ታገደ ። ከአራት ዓመት በኋላ ዘንድሮ እንዲታተም ተፈቀደ ። 

    ” የበልግ” መታገድ አንዳች የተጨበጠ ምክንያት : ላልነበረው አያሌ የሕዝብና የጋዜጦች ሐተታ : ትችት : ጥያቄና አቤቱታ ቢያስከትልም የተሰጠ መልስ ግን አልነበረም : እስካሁንም የለም ። ( ይህን ለማረጋገጥ በ 1954 ዓ.ም. በመስከረምና በጥቅምት ወር ውስጥ የወጡትን ጋዜጦች : በተለይም ” የኢትዮጲያ ድምፅ” 6 ኛውን ዓመት : ቁ. 271 – 281 – 284 – 286 መመልከት ለምሳሌ ያህል ይበቃል ። 

    “የበልግን” ድርሰት  ዛሬ ከስድስት ዓመት በኋላ በማተሚያው ጊዜ ሳነበው : ሊሻሻል የሚገባው የጽሑፍም ሆነ የአቀራረብ ግድፈት አልፎ አልፎ ቢታይበትም ፤ እርማቱ የቀድሞውን ቴያትር የየግብር ተካፋዮች ባሕርይ “ካራክተሪስትቲክስ” እስኪለውጠው ድረስ ባይጎላም አንዳንድ ይፋ የሆኑ ስህተቶችን አስተካክዬ ፤ ሌላውን የማይጎዳ ጥቃቅን ማሻሻያ ግን ዳግመኛ በሚታተምበት ጊዜ ከተፈላጊው ሐተታ ጋር አቃናዋለሁ በማለትና ፤ በተለይም : የመጀመሪያውን ንድፍ እንደነበረ አትሜ ለአንባቢዎቼ  ለማቅረብ በመፍቀዴ ምክንያት ብቻ አላጤንኩበትም። 

    በመስከረም 19 ቀን 1954 ዓ.ም. ዓርብ ማታ በተከፈተ ጊዜ ፤  ለማ ወርቄ እንደ አወናባጁ ጠበቃ እንደ ፈይሳ ፤ ነጋሽ ዘለቀ  እንደ ታታሪው ደራሲ እንደ አባተ ፤ ጌታቸው ደባልቄ እንደ ወፈፌው ሰዓሊ ኅሩይ ፤ ሶፊያ ይልማ እንደ አላዋቂዋ መስዕዋት እንደ ጌራ ወርቅ ፤ ሃብቱ ኃብተማርያም እንደ ቁጡው ቁማርተኛ እንደ ግዛው ፤ ጀምበሬ በላይ እንደ ግብዙ የኤኮኖሚክስ ተማሪ  እንደ አጥናፍ ፤ አበበ ይመኔ እንደ ልዝቡ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል እንደ ሻቃ ዳኜ ፤ አስናቀች ወርቁ እንደ ብኩኗ ቆንጆ እንደ ጽዮን ሆነው ተጫውተው ነበር ።”

በልግ 

ጸ . ገ . መ .

ጽሁፍ፥ሌይቲ